የተደራጁ እና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች ዐቃቤ ሕግ ዳይሬክቶሬት ጀነራል ተግባር እና ኃላፊነት

 ቀደም ሲል ይህ ተግባር በተለያዩ የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የስራ ክፍሎች በተለይም በቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች እና በዳይሬክቶሬት ደረጃ ተሰበጣጥረው ሲሰሩ የቆዩ ቢሆንም ከተደራጁ እና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀል ጉዳዮች ልዩ ባህርይ እና ውስብስብነት እንዲሁም የከፍተኛ አመራሩን ቀጥተኛ ክትትል እና ድጋፍ የሚጠይቅ ስራ መሆኑን እንዲሁም የስራ ቅብብሎሽ ለማስወገድ፣ በታችኛው መዋቅርም ያለው የጉዳዮች ጫና (ብዛት) አነስተኛ መሆኑ እንዲሁም የጉዳዮችን አያያዝ ወጥነት ማረጋገጥ አስፈላጊ መሆኑን ከግምት ውስጥ በማስገባት የየተደራጁ እና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀል ጉዳዮች ክትትል በማዕከል ደረጃ በዚህ ዳይሬክቶሬት ስር ተደራጅቷል፡፡

ይህ የስራ ክፍል ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ ሆኖ በስሩ የሽብርተኝነትና ተያያዥ ወንጀሎች ዐቃቤ ሕግ ማስተባባሪያ እና የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች ዐቃቤ ሕግ ማስተባባሪያን ይዟ የሚከተሉት ትግባር እና ሀላፊነት ይኖሩታል፡- 

የተደራጁ እና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን በተመለከተ የወንጀል ምርመራ እና ክርክር ሂደትን በበላይነት ከመመራት ባሻገር፡- 

  1. የተቋሙንና የዘርፉን ዕቅድ መነሻ በማድረግ የስራ ክፍሉን ተግባራት ያቅዳል፣ አፈፃጸማቸውን ይከታተላል ፣ድጋፍ ይሰጣል፤ 
  2. ስትራቴጂዎች፣ ፖሊሲዎችና ሕጎች ለመቅረጽ ግብዓት የሚሆኑ ምክረ ሀሳቦችን ያቀርባል፣ 
  3. ለስራ ክፍሉ የሚያስፈልገውን ሰብአዊ እና ቁሳዊ ግብአት እንዲሟላ ያደርጋል፣ ስራ ላይ መዋሉን ይከታተላል፣ 
  4. የስራ ክፍሉ ተግባራት የሚመሩበትን መመሪያዎች እንዲዘጋጁ ያደርጋል ፣ሲፀድቁም በአሰራሩ መሠረት መፈጸማቸውን ያረጋግጣል ፣ በየጊዜው እንዲሻሻሉ ሃሳብ ያቀርባል፤ 
  5. በስራ ክፍሉ ያሉ ባለሙያዎችን የክህሎት ክፍተት ለይቶ አቅማቸው የሚገነባበትን ስልጠናና ትምህርት እንዲያገኙ ያደርጋል፤የስራ ክፍሉን ሰራተኞችን የስራ አፈፃፀም ይመዝናል፤ 
  6. ከዘርፉ ኃላፊ ጋር በመመካከር ለስራ ክፍሉ ተልእኮ መሳካት አስተዋፅኦ ካላቸው ተቋማትና የሥራ ክፍሎች ጋር የሥራ ግንኙነቶችን ይፈጥራል፣ በቅንጅት ይሰራል፤ 
  7. ከስራ ክፍሉ ተልእኮ ጋር የተያያዙ መረጃዎችን እና ምርጥ ተሞክሮዎችን ያደራጃል፣ 
  8. ለስራ ክፍሉ የሚቀርቡ አቤቱታዎችን እና ቅሬታዎችን ተቀብሎ ያስተናግዳል ፣ ተገቢውን ምላሽ ይሰጣል፤ 
  9. የስራ ክፍሉን የስራ አፈፃፀም ይከታተላል፣ ይገመግማል፣ ከቡዱኖች ሪፖርት ይቀበላል፣ ግብረ መልስ ይሰጣል፣ የስራ አፈጻጸም ሪፖርት አዘጋጅቶ በወቅቱ ለሚመለከታቸው አካላት ያቀርባል፣ 
  10. በስራ ክፍሉ ተልእኮ የኅብረተሰብ ክፍሎች የሚሳተፉበት የሕዝብ መድረክ ያዘጋጃል፣ያሳትፋል፣ 
  11. የዳይሬክቶሬቱ ሠራተኞች በተቀመጡ እሴቶች መሠረት በስነምግባር እና በባለቤትነት ስሜት እንዲሰሩ እና ውጤታማ እንዲሆኑ የኮቺንግ (Coaching) ሥራ ያከናውናል፣ በስራ ክፍሉ ያሉትን ሰራተኞች በስነምግባር እንዲገነቡ ያደርጋል፣ ጥሰት ሲፈፀም ተጠያቂነት እንዲሰፍን ያደርጋል፤ 

ከላይ ከተጠቀሱት ለተቋሙ የስራ ክፍሎች በወል ከተሰጡ ተግባር እና ኃላፊነቶች በተጨማሪ በሚከተሉት የወንጀል ጉዳዮችን አስመልከቶ በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ማቋቋሚያ አዋጅ የተሰጡትን ተግባር እና ኃላፊነትን ከዚህ በታች በተዘረዘሩት የወንጀል ጉዳዮች ላይ የሚተገበር ሲሆን፡- 

በዚህ የሥራ ክፍል ስር ክትትል የሚደረግባቸው ጉዳዮች የሽብር እና ከሽብርተኝነት ጋር የተያያዙ የወንጀል ድርጊቶች፣ በተደራጀ ቡድን የሚፈፀሙ፣ ሁልግዜም ባይሆን አብዛኛውን ጊዜ ድንበር ተሻጋሪ የሆኑ እና በሀገር ላይ የሚያስከትሉት ጉዳት ከፍተኛ የሆኑትን እንዲሁም፡- አንዳንድ ወንጀሎች የሚያስከትሉት ጉዳት ከፍተኛ የሆኑና ሀገራዊ እንድምታ ያላቸው በመሆኑ ከዚህ ባህሪያቸው በመነጨ በዚህ የሥራ ክፍል የሚይዛቸውና ክትትል የሚያደርግባቸው ሆኖ፡- 

በዳይሬክቶሬት ጀነራሉ የሚታዩ የወንጀል ጉዳዮች፡-

  1. በኢትዮጵያ የወንጀል ሕግ እና በፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅ ላይ የሽብር ወንጀሎች ተብለው የተዘረዘሩ ወንጀሎች፣ 
  2. በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረት ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብ (Money Laundering) እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳት (Financing of Terrorism) ጋር ተያይዞ የሚፈፀሙ ወንጀሎች (አዋጅ ቁጥር 780/2005 
  3. የኮምፒዩተር ወንጀል አዋጅ ቁጥር 958/2008ን በመተላለፍ የሚፈጸሙ ወንጀሎች፣ 
  4. ዓለም አቀፍ ሕጎችን በመጣስ የሚፈፀሙ ወንጀሎች (የወንጀል ሕግ አንቀጽ 269- 283) በዚህ ውስጥ ዘር ማጥፋት፣ በሰላማዊ ሕዝብ ላይ የሚፈፀሙ የጦርነት ወንጀሎች ወ.ዘ.ተ. 
  5. በጦር መሳሪያ መነገድ /ማዘዋወር/፣ የተከለከለ ጦር መሣሪያ መያዝ (የወንጀል ሕግ አንቀጽ 481 ፣ 
  6. የጦር መሳሪያ አስተዳደር እና ቁጥጥር አዋጅ ቁጥር 1177/2012ን በመተላለፍ የሚፈጸሙ ወንጀሎች ፣ 
  7. በሁለት እና ከዚያ በላይ በሆኑ ብሔር ብሔረሰቦች ወይም ክልሎች መካከል ከተፈጠረ ግጭት ጋር ተያይዞ የሚፈፀሙ ወንጀሎች፣ 
  8. በሰው የመነገድ እና ሰውን በሕገ-ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር ወንጀሎች፣ 
  9. በወንጀል ህጉ አንቀጽ 525/1/፣ /2/ሀ/ ስር የሚወድቁ የአደገኛ ዕጽ ዝውውር፣ 
  10. በፖለቲካ ምክንያት ሰውን ማገት ወይንም መጥለፍ (የወንጀል ሕግ አንቀጽ 595)፤ 
  11. በውጭ አገር መንግስታት ላይ የሚደረጉ ወንጀሎች (የወንጀል ሕግ አንቀጽ 261- 266) በባለሥጣኖችና ዲኘሎማቶች የሚፈፀሙ ግድያዎች እና ሌሎች ወንጀሎችን ጨምሮ፣ 
  12. በመንግስት የውጭ ደህንነት እና በመከላከያ ኃይል ላይ የሚደረጉ ወንጀሎች (የወንጀል ሕግ አንቀጽ 246-252)- በዚህ ውስጥ በአገር ነጻነት ላይ የሚደረግ ወንጀል፣ የአገር መከላከያ ኃይልን መጉዳት፣ ክህዳትና የኢኮኖሚ ክህዳት፣ ከጠላት ጋር መተባበር እና ስለላ፣ 
  13. በሕገ-መንግስታዊ ሥርዓቱና በመንግስት የሀገር ውስጥ ደህንነት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች /የወንጀል ሕግ አንቀጽ 238-245/፣ 
  14. ሀገራዊ አንድምታ ያላቸው የምርጫ አዋጁን በመጣስ የሚፈጸሙ ወንጀሎች፣ (ለምሳሌ በተለያዩ ሚዲያዎች የምርጫ ውጤትን ከመተንበይ ጋር የተያያዙ)፣ 
  15. በማጓጓዣዎችና በመገናኛዎች ነጻነትና ፀጥታ ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች (የወንጀል ሕግ አንቀጽ 505-511)፣ 
  16. ከቴሌኮም ማጭበርበር ጋር በተያያዘ የሚፈፀሙ ወንጀሎች አዋጅ ቁጥር 761/2004፣ 
  17. በዋና ዋና የመሠረተ ልማት አውታሮች ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች (ለምሳሌ በኤሌትሪክ/በኃይል ማመንጪያና ማስተላለፊያ/፣ በቴሌ ኮምዩኒኬሽን፣ በባቡር…)፣ 
  18. የጥላቻ ንግግር እና የሀሰት መረጃ ማሰራጨት የሚከለክለውን አዋጅ በመተላለፍ የሚፈጸሙ ወንጀሎች 
  19. የሚዲያ እና ፕሬስ ሕግን በመጣስ የሚፈፀሙ ወንጀሎች፣ ከመገናኛ ብዙሀን እና መረጃ ነጻነት አዋጅ ጋር ተያይዞ በሰው ክብር እና መልካም ስም ላይ የሚፈጸሙ ሆነው በዐቃቤ ሕግ ክስ ሊቀርብባቸው የሚገባ ወንጀሎች፤ 
  20. የባንክ ስራን ከመስራት ጋር በተያያዘ የሚፈጸሙ ወንጀሎች (ከአራጣ ወንጀል ጋር ያልተያያዘ) 
  21. በተደራጁ እና ድንበር ተሸጋሪ ወንጀሎች የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረት ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብ እና ስለመርዳት፣ 
  22. በሌሎች ህጎች የሚወጡ የተደራጁ እና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀል ጉዳዮች፣ 
  23. በሌሎች የወንጀል ጉዳዮች ዐቃቤ ሕግ የስራ ክፍሎች ከሚታዩ ሌሎች የወንጀል ጉዳዮች ጋር የተደራጁ እና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀል ጉዳዮች በተደራቢነት የሚገኝ በሚሆንበት ጊዜ ከፍተኛ ቅጣት የሚያስከትለው ጉዳይ የተደራጁ እና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀል ክስ ሆኖ ሲገኝ በዚህ ዳይሬክቶሬት ተጠቃሎ ይታያል፡፡ 
  24. ከላይ በተጠቀሱት የወንጀል ጉዳዮች በፍርድ ቤት የተላለፈ የገንዘብ ቅጣትን በወንጀል ህጉ መሰረት ያስፈጽማል፣ 
  25. ከላይ የተዘረዘሩ የወንጀል ጉዳዮች አስፈላጊነቱ በዳየሬክቶሬቱ ሲታመንበት ለቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች በውክልና ሊሰጥ ይችላል፡፡ 

Department Lead

ዮሢያድ አበጀ በሀሩ

ዳይሬክተር ጀነራል