የኢኮኖሚ ወንጀል ጉዳዮች ዐቃቤ ሕግ ዳይሬክቶሬት ተግባር እና ኃላፊነት

ቀደም ሲል ይህ ተግባር በተለያዩ የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የስራ ክፍሎች በተለይም በቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች እና በዳይሬክቶሬት ደረጃ ተሰበጣጥረው ሲሰሩ የቆዩ ቢሆንም ከኢኮኖሚ ወንጀል ጉዳዮች ልዩ ባህርይ እና ውስብስብነት እንዲሁም የከፍተኛ አመራሩን ቀጥተኛ ክትትል እና ድጋፍ የሚጠይቅ ስራ መሆኑን በተጨማሪም የስራ ቅብብሎሽ ለማስወገድ፣ ከምርመራ አካላት ጋር የተናበበ አደረጃጀት የመኖሩ አስፈላጊነት እና የጉዳዮችን አያያዝ ወጥነት ማረጋገጥ አስፈላጊ መሆኑ ከግምት በማስገባት የኢኮኖሚ ወንጀል ጉዳዮች ክትትል በማዕከል ደረጃ በዚህ ዳይሬክቶሬት ስር ተጠቃሎ ተደራጅቷል፡፡

ይህ የስራ ክፍል ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ሆኖ በስሩ የግብር ወንጀል ጉዳዮች ዐቃቤ ሕግ ቡድን፣ የጉምሩክ ወንጀል ጉዳዮች ዐቃቤ ሕግ ቡድን፣ እና የሸማቾችና ልዩ ልዩ የኢኮኖሚ ወንጀል ጉዳዮች ዐቃቤ ሕግ ቡድንን ይዞ የሚከተሉት ተግባር እና ሀላፊነት ይኖሩታል፡- የኢኮኖሚ ወንጀሎችን በተመለከተ የወንጀል ምርመራ እና ክርክር ሂደትን በበላይነት ከመመራት ባሻገር 

  1. የተቋሙንና የዘርፉን ዕቅድ መነሻ በማድረግ የስራ ክፍሉን ተግባራት ያቅዳል፣ አፈፃጸማቸውን ይከታተላል ፣ድጋፍ ይሰጣል፤ 
  2. ከስራ ክፍሉ ጋር ስትራቴጂዎች፣ ፖሊሲዎችና ሕጎች ለመቅረጽ ግብዓት የሚሆኑ ምክረ ሀሳቦችን ያቀርባል፣ 
  3. ለስራ ክፍሉ የሚያስፈልገውን ሰብአዊ እና ቁሳዊ ግብአት እንዲሟላ ያደርጋል፣ ስራ ላይ መዋሉን ይከታተላል፣ 
  4. የስራ ክፍሉ ተግባራት የሚመሩበትን መመሪያዎች እንዲዘጋጁ ያደርጋል ፣ሲፀድቁም በአሰራሩ መሠረት መፈጸማቸውን ያረጋግጣል ፣ በየጊዜው እንዲሻሻሉ ሃሳብ ያቀርባል፤ 
  5. በስራ ክፍሉ ያሉ ባለሙያዎችን የክህሎት ክፍተት ለይቶ አቅማቸው የሚገነባበትን ስልጠናና ትምህርት እንዲያገኙ ያደርጋል፤የስራ ክፍሉን ሰራተኞችን የስራ አፈፃፀም ይመዝናል፤ 
  6. ከዘርፉ ኃላፊ ጋር በመመካከር ለስራ ክፍሉ ተልእኮ መሳካት አስተዋፅኦ ካላቸው ተቋማትና የሥራ ክፍሎች ጋር የሥራ ግንኙነቶችን ይፈጥራል፣ በቅንጅት ይሰራል፤ 
  7. ከስራ ክፍሉ ተልእኮ ጋር የተያያዙ መረጃዎችን እና ምርጥ ተሞክሮዎችን ያደራጃል፣ 
  8. ለስራ ክፍሉ የሚቀርቡ አቤቱታዎችን እና ቅሬታዎችን ተቀብሎ ያስተናግዳል ፣ ተገቢውን ምላሽ ይሰጣል፤ 
  9. የስራ ክፍሉን የስራ አፈፃፀም ይከታተላል፣ ይገመግማል፣ ከቡዱኖች ሪፖርት ይቀበላል ፣ ግብረ መልስ ይሰጣል፣ የስራ አፈጻጸም ሪፖርት አዘጋጅቶ በወቅቱ ለሚመለከታቸው አካላት ያቀርባል፣ 
  10. በስራ ክፍሉ ተልእኮ የኅብረተሰብ ክፍሎች የሚሳተፉበት የሕዝብ መድረክ ያዘጋጃል፣ያሳትፋል፣ 
  11. የዳይሬክቶሬቱ ሠራተኞች በተቀመጡ እሴቶች መሠረት በስነምግባር እና በባለቤትነት ስሜት እንዲሰሩ እና ውጤታማ እንዲሆኑ የኮቺንግ (Coaching) ሥራ ያከናውናል፣ በስራ ክፍሉ ያሉትን ሰራተኞች በስነምግባር እንዲገነቡ ያደርጋል፣ ጥሰት ሲፈፀም ተጠያቂነት እንዲሰፍን ያደርጋል፤ 

ከላይ ከተዘረዘሩት ለተቋሙ የስራ ክፍሎች በወል ከተሰጡ ተግባር እና ኃላፊነቶች በተጨማሪ በሚከተሉት የወንጀል ጉዳዮች ክትትልን አስመልከቶ በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ማቋቋሚያ አዋጅ የተሰጡትን ተግባር እና ኃላፊነትን በተዘረዘሩት የወንጀል ጉዳዮች ላይ የሚያስፈፀም ሲሆን፡- 

በዚህ ዳይሬክቶሬት ስር የሚታዩ የወንጀል ጉዳዮች ኢኮኖሚያዊ ይዘት ያላቸዉ ሆነዉ በሀገር፣ በመንግስት፣ እንዲሁም በግለሰቦች ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ወንጀሎች ሆነው የሚታዩት፡- 

  1. ከታክስ እና ጉምሩክ ጋር የተያያዙ እና በሀገር እና በመንግስት ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ላይ ጉዳት የሚያደርሱ፣ 
  2. ከንግድ ዉድድር እና የሸማቾች መብት ጋር የተገናኙ ድርጊቶች ሆነዉ በሀገሪቱ ዉስጥ በሚደረጉ የንግድ እንቅስቃሴ ዉስጥ ያልተገቡና ህገ-ወጥ ድርጊት በመፈፀም ትክክለኛዉንና ህጋዊዉን አካሄድ በማዛባት የህጋዊዉን ነጋዴ፣ የሸማቹን መብት፣ እንዲሁም የመንግስትና የህዝብን ኢኮኖሚያዊ መብቶች የሚጎዱ፣ 
  3. ከንግድ ምዝገባና ፍቃድ ጋር በተያያዘ የሚፈፅሙ ወንጀሎች የንግድ ምዝገባ አፈጻጸምና የንግድ ሥራ ፈቃድ አሰጣጥ ስርዓት የነፃ ገበያ ኢኮኖሚን ለማራመድና የኢኮኖዊ እድገትን ለማስገኘት በሚያስችል መልኩ እዳይካሄዱ የሚያደርጉ እና በህጋዊ የንግዱ ማህበረሰብ ብሎም በሀገር ላይ ኢኮኖሚያዊ ጉዳት የሚያስከትሉ ወንጀሎች፣ 
  4. በወንጀል ህጋችን እና በተለያዩ አዋጆች ዉስጥ የተጠቀሱ በግለሰብ፣ በመንግስት እና በሀገር ንብረት፣ ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞች ላይ የሚፈፀሙ እና ጉዳት የሚያደርሱ ዋና ዋና ወንጀሎች ሆነው ዝርዝሩ ከዚህ በታች ቀርቧል፡-
    1. ሰነዶችን፣ መለያዎች ወደ ሀሰተኛ መለወጥ እና አስመስሎ መሥራት ወንጀሎች፣ 
    2. በተደራጀ መንገድ የሚፈፀሙ የኮንትሮባንድ ወንጀሎች፣ 
    3. የንግድ ማጭበርበር /ውስብስብ/ወንጀሎች፣ 
    4. በተደራጀ መንገድ የሚፈፀሙ እሽግ መፍታት እና ምልክቶችን ማንሳት ወንጀሎች፣ 
    5. በንግድ ድርጅቶች የሚፈፀሙ ወንጀሎች፣ 
    6. የጉምሩክ ቁጥጥርን ማሰናከል ወንጀል፣ 
    7. መደበኛ የኮንትሮባንድ ወንጀሎች፣ 
    8. የአጓጓዥ ግዴታዎችን በመጣስ የሚፈፀሙ ወንጀሎች፣ 
    9. ከኤሌክትሮኒክስ መረጃዎች ልውውጥ ጋር የተያያዙ ወንጀሎች፣ 
    10. መደበኛ እሽግ መፍታት እና ምልክቶች ማንሳት ወንጀል፣ 
    11. ሀሰተኛ ወይም አሳሳች መግለጫና የተጭበረበሩ ሰነዶች ወንጀሎች፣ 
    12. ከህገ-ወጥ ደረሰኞች ጋር የተያያዙ ወንጀሎች፣ 
    13. ህገ-ወጥ ተመላሽ ወይም ማካካሻ ጋር የተያያዙ ወንጀሎች፣ 
    14. ታክስ ስወራ ወይም ማጭበርበር ወንጀሎች፣ 
    15. የታክስ ወንጀልን መርዳት ወይም ማበረታታት፣ 
    16. በግብር ባለስልጣኑ ያልተፈቀደ ማሽን መጠቀም፣ 
    17. በግብር ባለስልጣኑ ያልተፈቀደ ሶፍትዌር ለገበያ ማዋል፣ 
    18. ፈቃድ ሳይኖር ማሽን ወይም ሶፍትዌር ማቅረብ፣ 
    19. በድርጅቶች አማካኝነት የሚፈፀሙ የታክስ ወንጀሎች፣ 
    20. ከግብር ከፋይ የመለያ ቁጥር ጋር የተያያዙ ወንጀሎች፣ 
    21. በአንድ ግብይት የተለያዩ ዋጋዎችን መመዝገብ፣ 
    22. ግብይት ሳይፈፀም ደረሰኝ መስጠት፣ 
    23. ያለሚኒስቴሩ ፈቃድ ደረሰኝ ማሳተም፣ 
    24. ለተጨማሪ እሴት ታክስ ሳይመዘገብ ደረሰኝ መስጠት፣ 
    25. ተጨማሪ እሴት ታክስ፣ ዴቢት ወይም ክሬዲት ወንጀሎች፣ 
    26. ከቴምብር ቀረጥ ጋር የተያያዙ ወንጀሎች፣ 
    27. ታክስ ለማስከፈል ከሚወሰዱ እርምጃዎች ጋር የተያያዙ ወንጀሎች፣ 
    28. የታክስ ህጎች አፈጻፀም እና አስተዳደሩን ማሰናከል፣ 
    29. ስልጣን ሳይኖር ታክስ መሰብሰብ፣ 
    30. የታክስ ወንጀል እንዲፈፀም መርዳት ወይም ማበረታታት፣ 
    31. ከታክስ ይግባኝ ኮሚሽን ጋር የተያያዙ ወንጀሎች፣ 
    32. በታክስ ወኪሎች የሚፈፀሙ ወንጀሎች፣ 
    33. ከሽያጭ መመዝገቢያ መሳሪያ ጋር የተያያዙ ወንጀሎች፣ 
    34. በንግድ ምዝገባ እና ፈቃድ አዋጅ ቁጥር 980/2008 መሠረት የንግድ ሚ/ር እና ሌሎች ሚ/ር መ/ቤቶች እንዲሁም የፌዴራል ተቋማት የንግድ ፈቃድ በሚሰጧቸው የንግድ ድርጅቶች የሚፈፀሙ የፀረ-ውድድር ተግባራት እና የሸማቾች ጥበቃን የሚመለከቱ ወንጀሎች /የግል ድርጅቶች፣ ኃላፊነት የተወሰነ የግል ማህበራት እና አክሲዮን ማህበራት ጨምሮ/፣ 
    35. ከፒራሚድ ሽያጭ ስልት /ኔትዎርክ ማርኬቲኒግ/ ጋር በተያያዘ የሚፈፀሙ ወንጀሎች፣ 
    36. አስገዳጅ የጥራት ደረጃ ምልክትን መጠቀም ሲኖርባቸው ያለመጠቀም፣ የጥራት ደረጃቸው የወረደ የንግድ ዕቃዎችን እና አገልግሎቶችን የማምረት ወይም የማስመጣት ወይም የማከፋፈል ድርጊቶች እና በሚዲያ ሀሰተኛ ወይም የተሳሳተ ማስታወቂያ የማስተላለፍ ድርጊት ጋር በተያያዘ የሚፈፀሙ ወንጀሎች፣ 
    37. ከንግድ ምልክት እና ሌሎች የአዕምሯዊ ንብረት ጥበቃ ጋር በተያያዙ የሚፈፀሙ ወንጀሎች፣ 
    38. በአዋጅ 980/2008 የተቀመጡ ድንጋጌዎች ጋር በተያያዙ የሚፈፀሙ ወንጀሎች 
    39. በወንጀል ሕግ ርዕስ ሶስት ስር ከአንቀጽ 343- 354 ድረስ የተገለፁ በመንግስት የኢኮኖሚ እና የገንዘብ ጥቅሞች ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች፣ 
    40. በወንጀል ሕግ ርዕስ አምስት ስር ከአንቀጽ 356-362 ድረስ የተገለፁ የታወቁ የገንዘቦች፣ የግዴታ ወይም የዋስትና ሰነዶች ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች፣ 
    41. የአራጣ ወንጀሎች፣ 
    42. የከበሩ ማዕድናት ዝውውር ወንጀሎች፣ 
    43. የገንዘብ ዝውውር ወንጀል /ሀሰተኛ ገንዘብ ህትመትና የውጪ ሀገር ገንዘብ ዝውውር ወንጀል/፣ 
    44. በኢኮኖሚ ወንጀሎች የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረት ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብ እና ስለመርዳት፣ 
    45. በሌሎች የወንጀል ጉዳዮች ዐቃቤ ሕግ የስራ ክፍሎች ከሚታዩ ሌሎች የወንጀል ጉዳዮች ጋር የኢኮኖሚ ወንጀል ጉዳዮች በተደራቢነት የሚገኝ በሚሆን ጊዜ ከፍተኛ ቅጣት የሚያስከትለው ጉዳይ የኢኮኖሚ ወንጀል ክሱ ሆኖ ሲገኝ በዚህ ዳይሬክቶሬት ስር ተጠቃሎ ይታያል፡፡ 
  5. ከላይ በተጠቀሱት የወንጀል ጉዳዮች በፍርድ ቤት የተላለፈ የገንዘብ ቅጣትን በወንጀል ህጉ መሰረት ያስፈጽማል፣ 
  6. ከላይ የተዘረዘሩ የወንጀል ጉዳዮች አስፈላጊነቱ ሲታመንበት ለቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች በውክልና ሊሰጥ ይችላል፡፡ 

Department Lead

ሀና ግዛው ቶላ

ዳይሬክተር ጀነራል