የተቋሙ ስልጣንና ተግባር

የፍትህ ሚኒስቴር ስልጣን እና ተግባራት የሚመነጨው የፌዴራል መንግሥት አስፈፃሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን ከወጣው አዋጅ ቁጥር 1263/2014፣ በዚሁ አዋጅ የስም ለውጥ ተደርጎበት የፍትሕ ሚኒስቴር የሆነውን የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ተቋምን ለማቋቋም በወጣው አዋጅ ቁጥር 943/2008 እና ከሌሎች አዋጆች ነው፡፡

በዚህ አጭር ጽሁፍም እነኚህኑ የተቋ ስልጣን እና ተግባራት እንደሚከተለው ተዘርዝረዋል፡፡

 

1. የፍትህ ሚኒስቴር በአዋጅ ቁጥር 943/2008 እና 1263/2014 መሰረት የተሰጡት ስልጣንና ተግባራት

የፍትህ ሚኒስቴር  በሕግ ጉዳዮች የፌዴራል መንግስት ዋና አማካሪ እና ተወካይ ሆኖ ይሰራል፤

1. የወንጀል ጉዳይን በተመለከተ የፍትህ ሚኒስቴር ስልጣንና ተግባራት፦

የወንጀል ፍትህ ፖሊሲን የሚመለከታቸውን አካላት በማስተባበር ያዘጋጃል፤ ሲፀድቅም ተግባራዊነቱን ያስተባብራል፣ ይከታተላል፣ ያረጋግጣል፤

የወንጀል ክስ፣ የክርክርና የፍርድ ማስፈፀም ስራዎች የአሰራር ነፃነቱን የሚያስከብር የወንጀል ጉዳዮች ዘርፍ አደረጃጀትና አሰራር እንዲኖረው ይደርጋል፡፡

በሌሎች ህጎች ለፖሊስ የተሰጠው ስልጣን እንደተጠበቀ ሆኖ በፌዴራል ፍርድ ቤት ስልጣን  ስር የሚወድቅ የወንጀል ምርመራ እንዲጀመር ያደርጋል፣ ክትትልና ድጋፍ ያደርጋል፣

 በፌዴራል ፖሊስ ምርመራ ዘርፍ የሚከናወኑ የምርመራ ሥራዎችን ይመራል፣ ይከታተላል፣ ያስተባብራል፣ ሪፖርት እንዲቀርብለት ያደርጋል፤ (አዋጅ ቁጥር 1263/2014 አንቀጽ 40)፡፡

 የተጠናቀቁ የምርመራ መዝገቦችን ከሕግና ከማስረጃ አንፃር መርምሮ ውሳኔ ይሰጣል፤

የጥፋተኝነት ድርድር ይወስናል፣ ድርድር ያደርጋል፣ አማራጭ የመፍትሄ እርምጃ እንዲወሰድ ይወስናል፣ ተግባራዊነቱን ይከታተላል፤

የፌዴራል መንግስትን በመወከል የወንጀል ጉዳዩች ክስ ይመሰርታል፣ ይከራከራል፣ ለህዝብ ጥቅም አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው ክስ ያነሳል፣ የተነሳ ክስ እንዲቀጥል ያደርጋል።

ሀገራዊ ይዘት የሚኖረው ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩን በማማከር ክስ ስለሚያነሳበት አግባብ መመሪያ ያወጣል፤

ፍርድ ቤቶች በወንጀል ጉዳይ የሚሰጡዋቸው ውሳኔዎችና ትዕዛዞች መፈፀምና መከበራቸውን ይከታተላል፣ የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ ያደርጋል፤

በፍርድ ቤት የሚወሰኑ የወንጀል ቅጣቶች በአግባቡ እንዲፈፀሙ ለማድረግ የሚያስችሉ ሥርዓቶችን ያደራጃል ወይም መደራጀታቸውን ያረጋግጣል፤

ታራሚዎችን የማረምና ማነፅ ስራዎችን፣ በዘርፉ የሚደረጉ ጥናቶችንና የሚሰጡ ስልጠናዎችን፣ ከግብር ጋር የተያያዙ የይግባኝ ስራዎቸን፣ የሰነዶች ማረጋገጥና ምዝገባ ስራዎችን እና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን የሚመለከቱ ስራዎችን ያስተባብራል(አዋጅ ቁጥር 1263/2014 አንቀጽ 40)፡፡

የሞት ቅጣት ውሳኔዎችን ለኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት ያቀርባል፣ አፈፃፀሙን ይከታተላል።

2. የፍትሐ ብሔር ጉዳዮችን በተመለከተ የፍትህ ሚኒስቴር ስልጣንና ተግባር፦

ሀ/ በፌዴራል የመንግስት መሥሪያ ቤቶች የሕዝብ እና የፌዴራል መንግስት መብትና ጥቅም ወኪል ሆኖ ይከራከራል፣ ያስከብራል፣ እንዲከበሩ ያደርጋል፣ ይከታተላል፣ ይቆጣጠራል፤

ለ/ በግዙፍ የመንግስት ፕሮጀክቶች የውል ዝግጅት እና ድርድር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ያደርጋል፣ የሕዝብና የፌዴራል መንግስት መስሪያ ቤቶች ጥቅም ይጎዳል ብሎ ሲያምን በሌሎች ጉዳዮች ውል ዝግጅትና ድርድር ያደርጋል ወይም የሚመለከታቸውን አካላት ያማክራል፤

ሐ/ የፌዴራል መንግስት መስሪያ ቤትን በመወከል የፍትሐብሔር ክስ ይመሰርታል፤ በከሰሱበት ወይም በተከሰሱበት የፍትሐ ብሔር ጉዳዮች ላይ ክርክር ያደርጋል፤ በክርክር አመራር ላይ ለመሥሪያ ቤቶች አቅጣጫ ይሰጣል፣ በሕግ መሠረት ፍርድን ያስፈፅማል፤

መ/ የፌዴራል መንግስት መስሪያ ቤቶች እርስ በርሳቸው ያልተግባቡባቸው የፍትሐብሔር ጉዳዩች በፍርድ ቤት ወይም ከፍርድ ቤት ውጭ ባለ አማራጭ የክርክር መፍቻ መንገድ እንዲወሰን ውሳኔ ይሰጣል፣ በውሳኔው መሰረት መፈፀሙን ያረጋግጣል፤

ሠ/ የፌዴራል መንግስት መስሪያ ቤቶች እርስ በርሳቸው ባልተግባቡበት የፍትሐ ብሔር ጉዳይ ላይ ውሳኔ ይሰጣል፣ (አዋጅ ቁጥር 1263/2014 አንቀጽ 40)፡፡

ረ/ በፌዴራል ፍርድ ቤቶች የፍትሐብሔር ክስ ለመመሥረት የገንዘብ አቅም የሌላቸውን ዜጎች በተለይም ሴቶችን፣ ሕፃናትን፣ አካል ጉዳተኞችን እና አረጋውያንን ወክሎ ይከራከራል፤

ሰ/ የገንዘብ አቅም የሌላቸው የወንጀል ተጎጂ የሆኑ ተበዳዩች እንዲካሱ መልሰው እንዲቋቋሙ እንዲሁም ከጉዳቱ የተያያዙ የፍትሐ ብሔር ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ እነሱን በመወከል የፍትሐብሔር ክስ ያቀርባል ወይም ይደራደራል፤

ሸ/ የኢፌዲሪ መንግስት በዓለምአቀፍ የዳኝነትና ከፊል ዳኝነት አካላት በሚከስበት ወይም በሚከሰስበት ጉዳይ መንግስትን በመወከል እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመመካከር ክርክር ያደርጋል፤ ድርድር ያካሂዳል፤ ውሳኔውንም ያስፈፅማል፤

ቀ/ በሀገር ወስጥና በውጪ ሀገር የሚገኙ ከወንጀል ጋር የተገናኙ ንብረቶች የማስመለስ ስራዎችን ይሰራል፣ ያስተባብራል፤(አዋጅ ቁጥር 1263/2014 አንቀጽ 40)፡፡

 

3. የሕግ ጥናት፣ ማርቀቅ እና ማጠቃለል ሥራን በተመለከተ የፍትህ ሚኒስቴር ስልጣንና ተግባር፦

ሀ/ በፌዴራል መንግሥት የሚወጡ ሕጎች የሕግ ረቂቅ ዝግጅት ይሰራል፤ የመንግስት አካላት የሚያዘጋጁት ረቂቅ ሕግ ከሕገ መንግስቱና ከፌዴራል ሕጎች ጋር የተጣጣመ መሆኑን ያረጋግጣል፣ ለሚመለከታቸው ክፍሎችም አስተያየት ያቀርባል፤ በክልሎች ጥያቄ ሲቀርብለት የሕግ ረቂቆችን በማዘጋጀት ይረዳል፤

ለ/ የሕግ ማሻሻያ ጥናቶችን እንዲሁም የኮዲፊኬሽንና የፌዴራል ሕጐችን የማሰባሰብና ማጠቃለል ሥራ ይሰራል፤ የክልል ሕጎችን ያሰባስባል፣ እንደአስፈላጊነቱም እንዲጠቃለሉ ያደርጋል፤

ሐ/ ኢትዮጵያ የምትፈርመው ወይም የምትቀበለው ዓለም አቀፍ ስምምነት ሕገ መንግስቱን እና የአገሪቱን ሌሎች ሕግጋት ያገናዘበና ከብሔራዊ ጥቅም አንፃር ተቀባይነት ያለው መሆኑን ያረጋግጣል፤

 

4. የፌዴራል ሕጐች ተፈጻሚነትን ከመከታተል አንጻር ተቋሙ ያለው ስልጣን

የፌዴራል መንግስቱ ሕጐች ተግባራዊ መደረጋቸውን እና አተገባበራቸውም ወጥነት ያለው መሆኑን ያረጋግጣል፤ እንዲሁም አስፈፃሚ የፌዴራል መንግስት መስሪያ ቤቶች ሥራቸውን በሕግ መሰረት ማከናወናቸውን ያረጋግጣል፤

 

5. ከአቅም ግንባታ አንጻር የፍትሕ ሚኒስቴር ተግባር

 ሀ/ የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ለፌዴራል መንግስት ባለስልጣናት፣ ሹመኞች፣ ተመራጮች፣ ሰራተኞች እንዲሁም የግሉ ዘርፍ ተሳታፊዎች እንደየአስፈላጊነቱ የሕግ ሥልጠና ይሰጣል ወይም እንዲሰጥ ያደርጋል፤

ለ/ ዐቃቤያነ ሕግ ስለ ስራቸው ያላቸውን አመለካከት፣ እውቀትና ክህሎት በተከታታይ እና በየደረጃው ለማሳደግ ሥልጠና ይሰጣል ወይም ስልጠና እና ትምህርት እንዲሰጣቸው ያደርጋል፤ 

 

6. ሰብአዊ መብትን በተመለከተ የፍትህ ሚኒስተሩ ስልጣንና ተግባር፦

ሀ/ ነፃ የሕግ ድጋፍን አሰጣጥ ስትራቴጂዎችን ይቀርፃል፣ አፈፃፀሙን ይከታተላል፣ በመስኩ የሚሰማሩ አካላትን ያስተባብራል፤

ለ/ ብሔራዊ የሰብአዊ መብት የድርጊት መርሀ ግብርን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ያዘጋጃል፣ አፈፃፀሙን ይከታተላል፤ በአገር አቀፍ ደረጃ የሚመለከታቸውን አካላት ያስተባብራል፣ ለሚመለከታቸው አካላት ሪፖርት ያቀርባል፤

ሐ/ በፖሊስ ጣቢያና በማረሚያ ቤት ቁጥጥር ሥር ያሉ ሰዎችን ይጎበኛል፣ አያያዛቸው እና ቆይታቸው በሕግ መሰረት መፈጸሙን ያረጋግጣል፣ ሕገ ወጥ ተግባር እንዲታረም እና እርምጃ እንዲወሰድ ያደርጋል፤

መ/ የሰብአዊ መብት ትምህርት እና የንቃተ ሕግ ለማዳበር በተለያዩ ዘዴዎች ትምህርት ይሰጣል፤ በዘርፉ የተሰማሩ የሚመለከታቸውን አካላት ያስተባብራል፤

ሠ/ ኢትዮጵያ ያፀደቀቻቸውን ወይም የተቀበለቻቸውን ዓለም አቀፍና አህጉራዊ የሰብአዊ መብት ስምምነቶች አፈፃፀማቸውን ይከታተላል፣ ለሚነሱ ጉዳዮች እንደ አግባብነታቸው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመመካከር ምላሽ ይሰጣል፤ የስምምነቶቹን ብሔራዊ የአፈፃፀም ሪፖርት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር ያዘጋጃል፤

 

 

7. ስለ ሕግ ጥናት

ሀ/ አሰራሩን ውጤታማ ለማድረግ ጥናትና ምርምር ያደርጋል፤

ለ/ የወንጀል ፍትሕ መረጃዎችን መሰብሰብ፣ ማደራጀት፣ መተንተንና ማሰራጨት የሚያስችል ሥርዓት ይዘረጋል፣ ያስፈፅማል፤

 

8. በህግ ጉዳይ ዐለም ዐቀፍ ትብብርን ከመምራት አንጻር የተቋሙ ስልጣን

በፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ስልጣንና ተግባር ስር የተመለከተው እንደተጠበቀ ሆኖ በወንጀልና ፍትሐብሔር ጉዳዩች ዓለም አቀፍ ግንኙነትና ትብብር ያደርጋል፤

 

9. ከህግ ኦዲት እና ኢንስፔክሽን አንጻር የተቋሙ ተግባር

በዐቃቤያነ ሕግ የሚሰጡ ውሳኔዎች በሕግ መሰረት መከናወናቸውን የሚያረጋግጥ የኢንስፔክሽን ክፍል ያደራጃል፣ ጉድለቶችን በጥናት አስደግፎ ይለያል፤ በግኝቱ መሠረትም እንዲታረሙ ያደርጋል፣ እርምጃ ይወስዳል ወይም እንዲወሰድ ያደርጋል፣ መልካም ተሞክሮዎችን ያስፋፋል፤

 

2. በሌሎች ሕጎች ለኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ፍትህ ሚኒስቴር/ በቀድሞ ስያሜው ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የተሰጡ ስልጣን እና ተግባራትን

ለኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ፍትህ ሚኒስቴር ከታች በተዘረዘሩት አዋጆች ውስጥ በግልጽ ተደንግገው የተሰጡት ስልጣኖች እና ተግባራት ይገኛሉ፡፡ የአዋጆቹ አጭር ርዕስ እና የተቋሙ ስልጣን የሚመነጭባው አንቀጾች እንደሚከተለው ቀርበዋል፡፡

ሀ/ የተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አዋጅ ቁጥር 213/92

ለ/ የመገናኛ ብዙሃን አዋጅ ቁጥር 1238/2013 (አንቀፅ 85)

ሐ/ የምስክሮች እና ጠቋሚዎች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 699/2003

መ/ የይቅርታ አሰጣጥና አፈጻፀም አዋጅ ቁጥር 840/2006

ሠ/ የኮምፒውተር ወንጀል አዋጅ ቁጥር 958/2008 (አንቀጽ 25 (2) የኮምፒዩተር ዳታን   ስለማሰባሰብ)

ረ/ በሰው የመነገድ፣ ሰውን በህገ-ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀልን ለመከላከል የወጣው አዋጅ ቁጥር 1178/2012 (አንቀጽ 37 ሥለ ትብብር ጥምረት ጽ/ቤት ማቋቋም፣ አንቀጽ 38 ስለ ተቋሙ ኃላፊነት እና አንቀጽ 46 መመሪያ ስለማውጣት)

ሰ/ የፌዴራል አስተዳደር ሥነ-ስርዓት አዋጅ ቁጥር 1183/2012 (አንቀጽ 16 ስለመመሪያ ምዝገባ እና አንቀጽ 17 ስለመመሪያ ተደራሽነ)

ሸ/ በንግድ ውድድርና ሸማቾች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 813/2006 (እንደተሻሻለ) አንቀጽ 37 (1) ለ የወንጀል ክስ ስለመመስረት) እና በኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለስልጣን አዋጅ ቁጥር 551/1999 (እንደተሻሻለ) የተመለከቱት

ቀ/ የሽብር ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የወጣ አዋጅ ቁጠር 1176/2012 (አንቀጽ 17 (2) እና 38))

በ/ የፌዴራል መንግስት ፕሮጀክቶች አስተዳደርና አመራር አዋጅ ቁጥር 1210/2012 (አንቀፅ 23-ስለ ፍትህ ሚኒስቴር ኃላፊነት)

ተ/ የግልግል ዳኝነትን እና የዕርቅ አሰራር ስርዓትን ለመደንገግ የወጣ አዋጅ ቁጥር 1237/2013 (አንቀጽ 18 (2))

ቸ/ በውጭ አገራት ለተሰጡ የግልግል ዳኝነት ውሳኔዎች እውቅና የመስጠት እና የመፈጸም ስምምነትን ለማጽደቅ የወጣ አዋጅ ቁጥር 1184/2012 አንቀጽ 5